የ1ቆሮ 15፡20-28 ዐውድ፣ መልእክቱ ምንድነው?

በጌታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድማጮችን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዛሬ የማቀርበው የትምህርቱ ርዕስ ፣ መሰረት የሚያደርገው በ1ቆሮ 15፡ 20-28 ላይ ባለው ክፍል ላይ ይሆናል።
“ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ
ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ
ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤ በኋላም፥ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ
ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት
የሚሻረው ሞት ነው፤ ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን። ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ
ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት
ይገዛል።” 1ቆሮ 15፡ 20-28
ይህን ዐውድ ለመረዳት በዚህ ክፍል በውስጥ በጉልህ ለተዘረዘሩት ዋና ዋና ነጥቦች፣ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ከአጠቃላይ
የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አንጻር ለመረዳት መፍቀድ ይገባናል። በዚህ ጥቅስ መሰረት ይሄን ዐውድ ለማብራራት በአራት ክፍል
ለማሳየት እሞክራለሁ።


1. በዚህ ዐውድ ቅድሚያውን የሚይዘው ሐረግ “ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ፣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል”
የሚለው ነው።
በዚህ ክፍል ሁለት ሰው ተገልጿል ፣ አንደኛው ሰው ሞትን ያመታብን ሰው ሲግሆን፣ ሁእተኛው ሰው ደግሞ ትንሳዔ
ሙታንን ያመጣልን ሰው ነው።
ይህ ክፍል ለየት ባለ መልኩ የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው የሆነበትን ገጽታ በማጉላትና፡ ሰው የሆነበት ምክንያት ሊተነተን እንደሚገባ
የሚያሳይ ነው። ትንሳዔ ሙታን በሰው በኩል ሆኗል ስልሚል፣ ክርስቶስ በሰውነቱ ገጽታ የሰራውን ታላቅ ስራ በተጻፈው ልክ
እንድንገነዘበው በማድረግ ሁለተኛው ሰው ካስፈለገበት ምክንያቶች አንዱን የሚያብራራ ሲሆን፣ በፊተኛው ሰው በኩል
የመጣብን ሲሆን ሞት ሲሆን፣ ሁለተኛው ሰው ግን ሞትን በሞቱ በመሻር ትንሳኤ ሙታንን እንዳበሰረልን የሚስረዳ እውነት
ነው።
በሁለትኛው ሰው በኩል የተራልንን ስራ በጥልቀት የሚስረዱ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ፣ ለአብነት ያክል አንዳንዶቹን
እንደሚከተለው እንመለከታቸዋለን።
“ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር
ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ።” ሮሜ 5፡15
“ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን
በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል። የሙታንንም ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ እኵሌቶቹ አፌዙበት፥ እኵሌቶቹ ግን። ስለዚህ ነገር ሁለተኛ
እንሰማሃለን አሉት።” ሐዋ 17፡31-32 ። ከሙታን ያስነሳው ሰውነቱን እንጂ ሌላ አካል አይደለም።
“የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ
እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን
የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን።” 1ቆሮ 15፡47-49። ይህ ሰው ሁለተኛው ሰው እንደሚባለና ከፊተኛው ሰው የሚለይ
መሆኑን ይገለጻል።

“አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ
ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፤” 1ጢ 2፡5። ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ
የሆነ ገጽታ ብቻ ሳይሆን ፣ ሰው የሆነ ገጽታም እንዳለው የሚያስረዳ ድንቅ ማስረጃ ነው።
በእነዚህ ጥቅሶች መሰረት ከመዳናችን ጋር የተገናኙ ስራዎች ማለትም ፣ ቤዛነት፣ ትንሳኤ፣ መካከለኛ፣ የሚሉት ቃላቶች በሙሉ፣
በሁለተኛው ሰው በኩል የተከፈለውን ዋጋ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በኤፌ 1፡20-22 ላይ “ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው …ሁሉንም
ከእግሩ በታች አስገዛለት” ስለሚል፣ ሁሉን ያስገዛለት ከሙታን ላስነሳው ገጽታ በመሆኑ፤ ከሞት የተነሳው ገጽታ ደግሞ ሜኮት
ወይም አምላክነት ሳይሆን የሰውነቱን ገጽታ መሆኑን መረዳት እጅግ ጠቃሚ ነው።
2. “መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፥
ፍጻሜ ይሆናል።”
ይህን ሐረግ በተጻፈበት መንፈስ ለመረዳት የልጁ መንግስት ማለት ከተለመደው የመንግስት አወቃቀር እሳቤ ወጣ ያለ
መሆኑን ማወቅ በጣም ያስፈለጋል። ይህ መንግስት የአስተዳደር ወሰንን ወይም በመንግስቱ የሚካተቱ ሰራዊቶችንና
የስልጣን ተዋረድ የሚያመለክት አይደለም።
የልጁ መንግስትን ምንነት ካልተረዳን “ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ” የሚለው ሐረግ አስተዳደራዊ የስልጣን ርክክብ የሚደረግ
አድርገን ልናስብ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ የልጁ መንግስት ሲል ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ቆላ 1፡13ን ማንበብ እጅግ
ጠቃሚ ነው።
“እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።”
ቆላ 1፡13-14
በቆላ 1፡13 ላይ የልጁ መንግስት ማለት አስተዳደራዊ ግዛት ማለት ሳይሆን ፤የኃጢአታችንን ስርየት በማግኘት ከጨለማ ስልጣን
መዳናችንን ለማሳየት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ የልጁን መንግስት በዝርዝር ለማወቅ፣ የኃጢያት ስርየት ያገኘንበትን መንገዶች
ሁሉ ለመረዳት መፍቀድ ስለሚያስፈልግ፤ የኃጢአታችንን ስርየት ያገኘንበትን መንገድ በቃሉ እንደተጻፈው እንደሚከተለው
እዘረዝራለሁ፡-
 በኤፌ 1፡7 …በደሙ ኃጢያታችን ይሰረያል ይላል፣
 በዕብ 10፡10-18 … የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ በማቅረብ ኃጢአት እንደሚሰረይ ይገልጻል
 1ዮሐ 2፡12… ስለ ኢየሱስ ስም ኃጢአት እንደሚሰረይ ያስረዳል፣
በእነዚህ ጥቅሶች መሰረት የልጁ መንግስት ማለት፣ ኢየሱስ ክርቶስ በሰውነት በመገለጡ በደሙ በስጋውና በስሙ ለኃጢአታችን
ስርየት የሰራውን ስራ የሚያመለክት እንጂ አስተዳደራዊ መዋቅር አይደለም።
ከዚሁ ኃሳብ ጋር በተያያዘ “መንግስቱን ለአባቱ በሰጠ ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል” ማለት፣ የኃጢአት ስርየት ያገኘንበትን ደሙን፡
ስጋውንና ስሙን ሰብሰብ አድርጎ ለአብ ያስረክባል ማለት ሳይሆን፣ የኋለኛው ጠላት ከተሻረ ቦኋላ፡ የኃጢአት ስርየት
በምናገኝበት መንግስት ላይ ያለው ኃጢአትን የማስተሰረይ ስልጣን ፍጻሜ ይሆናል ማለት መሆኑን በቀላሉ መረዳት እንችላለን።
በተጨማሪም በ1ቆሮ 15፡24 መሰረት “መንግስቱን በሰጠ ጊዜ” እና “አለቅነትንም ሁሉና ስልጣንን ሁሉ፣ ኃእልንም በሻረ ጊዜ”
የሚሉት ሁለት ክስትተቶች በአንድ ወቅት የሚፈጸሙ ናቸው ። በዚህም ምክንያት መሻር ያለባቸው “አለቅነት፤ ስልጣናትና
ኃይላት” በክርስቶስ ደም፣ በክርስቶስ ስጋ፣ ሞትና ትንሳኤ የተገዙ ቢሆንም በዕብ 2፡ 8 ላይ “ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ
ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና አናይም” ተብሎ በተጻፈው መሰረት፣
የሚሻሩበትን ጊዜ እየጠበቁ በመሆናቸው መገዛታቸው አሁን የሚታይ አይደለም። በ1ቆሮ 15፡26 ላይ “የኋለኛው
ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” ተብሎ ስለተጻፈ ሞትን ጨምሮ (በዕብ 2፡6-9፣ በዕብ 2፡14-15፣ በኤፌ 1፡20-22 እና 1ጴጥ

3፡22) ከላይ የተገለጹት አለቅነት ስለጣናትና ኃይላት፣ መሻራቸውን የምናየው በቆላ 1፡13 ላይ እንደተጻፈው ፣
የኃጢአት ስርየት የምናገኝበት መንግስት ስራው በሚጠናቀቅበት ጊዜ መሆኑን እንረዳለን።
3. “ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ
በሁሉ ይሆን ዘንድ ልጁ ራሱ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል” የሚለው መልእክት የኢየሱስ ክርስቶስን ሁለቱን ገጽታዎች
የሚያሳይ ብቻ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ አምላክም (ገዢም) እንዲሁም ሰውም
(ተገዢም)፣ መሆኑ በግልጽ ተነግሮናል።
“ሁሉን ያስገዛ” እና “ሁሉ በሁሉ” ተብሎ የተገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ የማይታየውና የማይሞተው ገጽታ በመሆኑ (1ጢ 6፡14-
16፣ ራዕይ 1፡7-8፣ ፊል 3፡21 እና ቆላ 3፡11) ፣ ሁሉን ለራሱ የሚያስገዛበት አሰራር ያለው፣ ሁሉ በሁሉ የሆነ የነገስታት ንጉሥና
የጌቶች ጌታ የሆነው ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ፣ በ ሁለት የተለያዩ ገዢና ተገዢ አካአት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
የለም።
“ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ ያለ እድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ ትእዛዙን ጠብቅ፤ ያንም መገለጡን በራሱ ጊዜ ብፁዕና
ብቻውን የሆነ ገዥ፥ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ያሳያል። እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን
ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።” 1ጢ 6፡14-16
“እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም
ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።” ፊል
3፡21-22
“በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር
ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።” ቆላ 3፡11
“እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥
አሜን። ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።” ራዕይ 1፡7-8
4. “ሁሉ ከተገዙለት ቦኋላ …በዚያን ግዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል” የሚለው ቃል የሚያመለክተው፣ ሁሉ
እንዲገዙለት የተደረገው ለሌላ ሁለተኛ አካል ሳይሆን ለሞተው፣ ከሙታንም በድል የተነሳውን፣ ሁለተኛው ሰው ተብሎ
የተገለጸውን የኢየሱስ ክርስቶስን የሰውነት ገጽታ የሚያመለክት መሆኑ፤ በኤፌ 1፡20-22፣ በግልጽ ተብራርቷል፣
ምክንያቱም ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሆነ ተብሎ በ 1ቆ15፡20 ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም በዮሐ 2፡19-21
ላይ ከሙታን የተነሳው ገጽታ የሰውነቱ በተመቅደስ መሆኑ በግለጽ ተነግሮናል።
እግዚአብሔር ሁሉን ያስገዛው ከሙታን ላስነሳው “ልጁ” ወይም “ሰውነቱ” በመሆኑ በኤፌ 1፡20-22 ላይ “ክርስቶስንም
ከሙታን ሲያስነሣው …ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት” ተብሎ የተጻፈ ሲሆን፤ በሐዋ 17፡31 ላይ ከሙታን ያስነሳው
ያዘጋጅውን ሰው መሆኑን ፣ በ1ቆሮ 15፡20 ላይ ደግሞ “ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሆነ” ተብሎ የተጻፈ ሲሆን፣ እንዲሁም
በ1ተሰ 1፡9 ላይ “ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን” ተብሎ ተጽፍዋል። በእነዚህ ማስረጃዎች መሰረት እግዚአብሔር ሁሉን
ያስገዛው ከሙታን ላስነሳው ለ“ልጁ” ማለት “ለሰውነቱ” መሆኑን ከቃሉ መረዳት ይቻላል።
“ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር
ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ
የብርታቱ ጉልበት ይታያል፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው።” ኤፌ
1፡20-22
ነገር ግን አንዱ በአንድ ስፍራ። ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ወይስ ትጎበኘው ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? ከመላእክት
ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች
አስገዛህለት ብሎ መሰከረ። ሁሉን ከእርሱ በታች ባስገዛ ጊዜ ያልተገዛለት ምንም አልተወምና። አሁን ግን ሁሉ እንደ ተገዛለት ገና
አናይም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ፥ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ የነበረውን ኢየሱስን
ከሞት መከራ የተነሣ የክብርና የምስጋናን ዘውድ ተጭኖ እናየዋለን። ዕብ 2፡6-9
“እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ
ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ
ተካፈለ።” ዕብ 2፡14-15
“እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም
ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ
ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።” 1ተሰ 1፡9-10
“ኢየሱስም መልሶ። ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። ስለዚህ አይሁድ። ይህ
ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፥ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን? አሉት። እርሱ ግን ስለ
ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።” ዮሐ 2፡19-21
ከላይ በሰፊው ያየናቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ በ1ቆሮ 15 ቁጥር 28 ላይ “ልጁ” ተብሎ የተገለጸው
የሞተው፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው “ሰው” የሆነው ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የሚታየው ገጽታ ሲሆን ፤ በራዕይ 1፡8 መሰረት
ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላክ” በመሆኑ፣ “ሁሉን የሚገዛ” የተባለው የኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክነት
ገጽታ ነው።
ስለዚህ የ1ቆ15፡20-28 አጠቃላይ መልእክት፣ የልጁ መንግስት ኃጢያት የማስተሰረዩን ስራ ከፈጸመ ቦኋላ፣ “ልጁ” ወይም “ሰው”
ተብሎ የተገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ የሚታይ ገጽታ ፣ “ሁሉን ሚገዛ” ለተባለው ለኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክነት ገጽታ፡ አካልና
መገለጫ ሆኖ፡ በቆላ 2፡9 ላይ እንደተጻፈው የመለኮት ሁሉ በሰዉነት ተገልጦ ለዘላለም ይኖራል ማለት ነው።
ጌታ ኢየሱስ መጽሐፍትን ማስተዋል እንችል ዘንድ አእምሮአችንን ይክፈትለን። አሜን!!
ፓስተር በረከት ማቴዎስ

Responses

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish